በሪዮ የተመዘገበው ውጤት የስፖርቱን ውድቀት አያመለክትም-የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 26፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በሪዮ ኦሊምፒክ ያስመዘገበችው ውጤት የአገሪቱን ስፖርት ውድቀት እንደማያመለክት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አንበሳው እንየው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ በሪዮ ኦሎምፒክ ያገኘቻቸው ሜዳሊያዎች የአገሪቱን የስፖርት ደረጃ መውረድ አያሳዩም።

በኦሎምፒኩ የተመዘገበው ውጤት በወርቅ ሜዳሊያዎች ቁጥር ቢቀንስም፤ አገሪቱ በለንደን ኦሎምፒክ ካደረገችው ተሳትፎና የሜዳሊያዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ስለነበር ”ስፖርቱ ወድቋል” አያስብልም ብለዋል።

የአገሪቱን ስፖርት በዓይነትና በተሳትፎ መጠን ለማሳደግ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት፣ የስፖርት መሠረተ ልማት ለማስፋፋት፣ በአገር ውስጥ የስፖርት ቁሳቁስ ምርትና የባለሀብቶችን ተሳትፎ ለመጨመር የሚደረገው ጥረት የዕድገቱ መለኪያዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

የስፖርት ዕድገት መለኪያ የሜዳሊያዎች ብዛት ብቻ ከሆነ፤ በስፖርቱ አደጉ የተባሉት ሁሉ ስፖርታቸው ተዳክሟል ሊባል እንደማይችልም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በ31ኛው ኦሎምፒክ ያስመዘገበችው ውጤት ከባርሴሎና ኦሎምፒክ በኋላ ከተመዘገቡት የወርቅ ሜዳሊያዎች ብዛት አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተዋል።

ወደ ሪዮ ለተሰማራው ቡድን ሳይንሳዊና ተጨባጭ ስልጠና አለመሰጠት፣ ካለፉት ኦሎምፒኮች ምርጥ ተሞክሮዎችን አለመውሰድ፣ አትሌቶችን መሰረት ያላደረገ ዕቅድ መውጣቱ ለውጤቱ ማነስ ምክንያቶች መሆናቸውንም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል።

ስልጠናው በየጊዜው አለመመዘኑ፣ የወርቅ ሜዳሊያ ሊያመጡ የሚችሉ አትሌቶች በቡድኑ አለመካተት፣ በሥነ-ልቦናና የቡድን ስሜት ላይ አለመሰራቱ፣ ሳይንሳዊ መንገድ የተከተለ አመጋገብ አለመከተል ሌሎቹ ችግሮች መሆናቸውንም አስረድተዋል።

የቡድን መሪው በተደራጀ መልኩ አለመመራቱም የተጠበቀው ውጤት እንዳይገኝ አስተዋጽኦ ማድረጉን አቶ አንበሳው ተናግረዋል።

የታዋቂ አትሌቶች ጊዜያዊ ኮሚቴ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በባለሙያዎች እንዲደራጅ ባቀረበው ሐሳብ ላይ ተጠይቀውም ፌደሬሽኑ ያሉበትን የአሰራር ችግሮች ለማስተካከል እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ፌደሬሽኑ በሚያካሂደው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ ክልሎች በባለሙያዎች እንዲደራጁ፣ የተሻለ ዕውቀት ባለውና ስፖርቱን በሚደግፍ የሰው ኃይል እንዲመሩ ሚኒስቴሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በሪዮ ኦሎምፒክ በአትሌቲክስ፣ በውሃ ዋናና ብስክሌት ተሳትፎዋ አራት የወርቅ፣ አራት የብርና አራት የነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን ለማምጣት አቅዳ አንድ ወርቅ፣ ሁለት ብርና አምስት ነሐስ በጠቅላላው ስምንት ሜዳሊያዎችን ይዛ ተመልሳለች በማሉን ኢዜአ ዘግቧል።

Share this on:

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


*