አቶ ኤርሚያስ አመልጋ የሚያዙበት ገንዘብ ሳይኖር ቼክ በመፈረም ክስ ተመሰረተባቸው::

Ermias Amelga

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 19 ፣ 2008 – የቀድሞ የአክሰስ ሪል ስቴት ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ከ4 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ የሚያዙበት ገንዘብ ሳይኖር ቼክ በመፈረም ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው።

አቶ ኤርሚያስ ተጠርጥረው የተከሰሱበት ወንጀልም በክሱ በዝርዝር ተቀምጧል።

ይህም ተከሳሽ የሚያዙበት በቂ ገንዘብ አለመኖሩን እያወቁ ቀንና ወሩ በውል ባልታወቀ 2005 ዓ.ም፥ በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ቦሌ መድሀኒያለም አካባቢ በሚገኘው ቢሮ ውስጥ በዘመን ባንክ አክሲዮን ማህበር የተዘጋጀና ከባንኩ ዋና ቅርጫፍ ጥቅምት 29 ቀን 2005 ዓ.ም የሚመነዘሩ ደረቅ ቼክ መጻፍ የሚል ነው።

የተለያዩ የቼክ ቁጥር ላይ በተለያዩ አራት ቀናት በድምሩ 2 ሚሊየን 450 ሺህ ብር ለግል ተበዳይ ፍጹም አስፋው በመጻፍ፥ በሌላ በኩል ለሳምራዊት ጴጥሮስም በየካቲት 14ና መጋቢት 11 ቀን 2005 ዓ.ም የሚመለስ ከ822 ሺህ ብር በላይ ያለ በቂ ስንቅ ቼክ ጽፈዋል።

እንዲሁም ለግል ተበዳዮች ጽጌረዳ አበበ እና ለንጉሴ መንግስቱ ለእያንዳንዳቸው 500 ሺህ ብር፣ ለሳዲቅ አብዱልዋሂብ 255 ሺህ 534 ብር እና ለዶክተር ኤርሚያስ ሀብቴ 343 ሺህ 400 ብር በቂ ስንቅ ሳይኖር ቼክ መጻፋቸው በክሱ ተጠቅሷል።

ይህም በጠቅላላው አራት ሚሊየን 871 ሺህ 854 ብር በተወሰነ ቀን የሚመለስ በቼክ ላይ ጽፈው በተባለበት ቀን ሲታይ፥ በቂ ገንዘብ እንደሌለና ለግል ተበዳዮችም ክፍያው ሳይፈጸም መቅረቱ በክሱ ላይ ተጠቅሷል።

በዚህም ግለሰቡ በፈጸሙት የሚያዙበት ገንዝብ ሳይኖር ቼክ ማውጣት ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ክሱን ተከትሎ አቶ ኤርሚያስ ከጠበቆቻቸው ጋር ዛሬ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው፥ የደረሳቸውን ክስ እንዲመለከቱና መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ በችሎቱ ተነግሯቸዋል።

የተከሳሽ ጠበቆች ደንበኛቸው ክሱ ዋስትና የማያስከለክል በመሆኑ ደንበኛቸው ዋስትና እንዲፈቀድላቸውና ጉዳያቸውን ውጪ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል።

አቃቢ ህግም ተከሳሽ ሊሸሹ ይችላሉና መሰል ምክንያቶችን በማቅረብ ዋስትናው ውድቅ እንዲደረግ አመልክቷል።

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን የዋስትና ክርክር መርምሮ፥ ትዕዛዝ ለመስጠትና በክሱ ላይ መቃወሚያ ካለ ለመስማት ለሀሙስ መጋቢት 22 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አቶ ኤርሚያስ በተጠረጠሩበት የማታለል ወንጀል የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን የ500 ሺህ ብር ዋስትና መርማሪ ፖሊስ ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት ይግባኝ ማለቱ ይታወሳል።

ዛሬ ይግባኙን ተከትሎ ከሁለቱም ክርክር የተደረገበት ሲሆን፥ ችሎቱ የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ዋስትና በእገዳ በማቆየት የፊታችን አርብ መጋቢት 23 ቀን 2008 ዓ.ም ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ኤፍ ቢ ሲ

Share this on:

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


*

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.