ኢትዮጵያ በአሁኑ ሩጫዋ ከቀጠለች በ2017 መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ትሆናለች- የዓለም ባንክ

Ethiopian great run poster

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 13 ፣ 2008 – የዓለም ባንክ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ከአውሮፓውያኑ 2004 እስከ 2014 ኢትዮጵያ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርቷ /ጂ ዲ ፒ/ የ10 ነጥብ 9 በመቶ በአማካይ ማደጉን አስታውቋል።

አገሪቱ በዚሁ ፍጥነት የኢኮኖሚ እድገታን ማስቀጠል ከቻለች በአውሮፓውያኑ 2025 ላይ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ለመሆን ያስቀመጠችውን ግብ እንደምታሳካ ነው የገለፀው።

ባንኩ በአገሪቱ አስገራሚ የምጥኔ ሀብት እድገት ጀርባ ያሉ ጉዳዮችን በተመለከተበት እና ዛሬ ይፋ ባደረገው “የኢትዮጵያ ታላቅ ሩጫ” በሚል ርእስ ባወጣው ሪፖርት ላይ እንዳመለከተው፥ ለእድገቷ ሰፊ የመንግስት የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት እና ውጫዊ ምቹ ሁኔታዎችን በምክንያትነት አንስቷል።

ከአውሮፓውያኑ 1992 ጀምሮ አገሪቱ በኢኮኖሚዋ ላይ ለውጥን እያሳየች መምጣቷን ያመለከተው ባንኩ፥ ከአውሮፓውያኑ 2004 ጀምሮ ያሳየችው እድገት ግን አስገራሚ ነው ብሏል።

በእነዚህ ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻን ከድህንት ማውጣት ችላለች፤ የዜጎችን በህይወት የመቆያ እድሜ ከፍ አድርጋለች፤ የእናቶች እና ህፃናት ሞትንም ቀንሳለች።

እንደ ባንኩ ሪፖርት በአውሮፓውያኑ ከ2000 እስከ 2011 ድረስ አገሪቱ ድህነትን በ44 በመቶ መቀነስ ችላለች።

ለምጣኔ ሀብት እድገቱ የአገልግሎት እና ግብርና ኢንዱሰትሪዎች የመሪነት ሚናቸውን መጫወታቸውን በማንሳት፥ ለአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት /ጂ ዲ ፒ/ እድገት የአገልግሎት ኢንዱስትሪ የ5 ነጥብ 4 በመቶ እና ግብርና የ3 ነጥብ 6 በመቶ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።

ከግብርና ዘርፍ ወደ አገልግሎት እና ግንባታ ዘርፍ ያለው የሰው ሀይል ፍሰቱም የዜጎች የነብስ ወከፍ ገቢ ከአውሮፓውያኑ 2005 እስከ 2013 ድረስ በ13 በመቶ እንዲያድግ አስተዋፅኦ ማበርከቱንም ነው በባንኩ ሪፖርት ላይ የተመለከተው።

ባንኩ ኢትዮጵያ ይህን እድገቷን ለማስቀጠል ብትተገብር ብሎ የራሱን ምክረ ሀሳብ አስቀምጧል።

ለምጣኔ ሀብት እድገቱ ዘላቂነት የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ቁልፍ በመሆኑ ይህ ዘርፍ በተለይም የፋይናንስ ምንጭ እንዲያገኝ በማድረግ ድጋፍ ሊሰጠው ይገባል ብሏል።

አገሪቱ ለምታከናውነው የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት አሁን ካሉት በተጨማሪ ሌሎች የፋይናንስ ምንጮችንም እንደትመለከት መክሯል።

የፋይናንስ ኢንዱስትሪዋንም የበለጠ በማዘመን የፋይናንስ ተቋማት ተደራሽነትን ለማሳደግ መስራት አለባትም ብሏል።

ኤፍ ቢ ሲ

Share this on:

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


*