20ኛው የግንቦት 20 የድል በዓል

"ginbot addis ababa ethiopia"
የግንቦት 20 ድል 20ኛ ዓመት የድል በዓል በ አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በትናንትናው ዕለት በመላ አገሪቱ የደርግ ሥርዓትን የገረሰሰበትን የግንቦት 20 ድል 20ኛ ዓመት በማስመልከት ሚሊዮኖችን በማሰለፍ አክብሯል፡፡

እዚህ አዲስ አበባ የከተማው ኗሪዎች፣ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች በመስቀል አደባባይ በከፍተኛ ቁጥር ተገኝተው ዕለቱን ዘክረዋል፡፡ ግንቦት 1983 ዓ.ም. በድል አድራጊነት መላ አገሪቱን መቆጣጠሩን ያበሰበረበት 20ኛው የድል በዓል አከባበርን በተመለከተ ኢሕአዴግ ባወጣው መግለጫ፣ የአገሪቱ ሕዝቦች የግንቦት 20 ድል ዓላማዎችን ለማሳካት ባለፉት 20 ዓመታት ባደረጉት ሁለንተናዊ ትግል፣ በሁሉም መስኮች አመርቂ ድሎችን ለማስመዝገብ መብቃታቸውን አስታውቋል፡፡

በግንቦት 20 ድል መንፈስ ተግባራዊ ለማድረግ የተጀመሩ ርብርቦች መቀጠል እንደሚኖርባቸውና ታላቁ የህዳሴ ግድብም የአገሪቱን ሕዝቦች በአንድ የልማትና የዕድገት መንፈስ ያስተሳሰረ እጅግ አኩሪ የግንቦት 20 የድል ገፀ በረከት ነው ብሏል፡፡ ኢሕአዴግ ለመላው የአገሪቱ ሕዝቦች ባደረገው ጥሪ፣ ‹‹ዛሬም እንደ ትናንቱ ከእናንተ ጎን በመሰለፍ ተሳትፏችሁንና ተጠቃሚነታችሁን ለማረጋገጥ አበክሮ ለመሥራትና የጀመረውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በድል ለማጠናቀቅ፣ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመሩን አንግቦ የመሪነት ሚናውን ለመወጣት ያለውን ቁርጠኝነት በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል፤›› ሲል ገልጿል፡፡

በመቀጠልም፣ ‹‹በእኩልነትና በመፈቃቀድ የገነባችሁት ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የዴሞክራሲያዊ አንድነታችሁ፣ የልማታችሁና የሰላማችሁ መሠረት ሊሆን ችሏል፤›› ብሎ፣ ‹‹የጀመራችሁትን ስኬታማ ጉዞ ለማደናቀፍ ከውስጥም ከውጭም የሚያሴሩባችሁን ኃይሎች በመመከት ወደፊት እንድትራመዱ ኢሕአዴግ ጥሪውን ያቀርብላችኋል፤›› በማለት የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞቱን አስተላልፏል፡፡

Share this on:

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*


*

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.